Governmental Organizations
የአማራ ብሔራዊይ ክልላዊ መንግስት አመራር አካዳሚ
ተልዕኮ
ክልሉን ሊያሣድጉ የሚችሉ ብስለት ያላቸውን ሣይንሳዊና ዘመን ተሻጋሪ ሃሳቦች በማመንጨት የትምህርትና ስልጠና፣ የምርምርና ምክር አገልግሎት በመስጠት የህዳሴውን ጉዞ ቀጣይነት የሚያረጋግጥ፣የህዝብን ጥያቄ ፈጥኖ የሚረዳና ምላሽ የሚሰጥ ብቃት ያለው የፖለቲካ አመራርና ሌሎች የልማት ኃይሎችን በማፍራት ለሃገሪቱ ዘላቂ ልማትና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተዋጽኦ ማድረግ ነው ፡፡
ራዕይ
አካዳሚው በ2017 በፖለቲካዊ አመራር ጥበብ በአገር ደረጃ የለውጥና የብቃት ሞዴል ማዕከል ሆኖ ማየት፣
የአመራር አካዳሚው ሥልጣንና ተግባር
አካዳሚው የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት አሉት
በሀገሪቱ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ዙሪያ የየደረጃውን አመራርና ፈፃሚ ሀይሎች በብቃትና በጥራት ለማፍራት የሚያስችሉና በዘመናዊ የጥናት፣ የምርምር፣ የምልከታ፣ የትንተና እና የሥርፀት ሥራዎች የተደገፉ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ትምህርትና ስልጠናዎችን ይሰጣል፣ ለዚሁ የሚያገለግሉ ሞጁሎችን ያዘጋጃል፣ ሌሎች ተያያዥነት ያላቸውን የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ያደራጃል፤
ክልላዊ እና ሀገር አቀፍ የልማት ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን፣ መርሆዎችንና ዓላማዎችን መነሻ በማድረግ ዝርዝር የትምህርትና የስልጠና መርሀ-ግብሮችን ይቀርፃል፣ በቦርዱ ሲፀድቁለትም በስራ ላይ እንዲውሉ ያደርጋል፤
የሚሰጣቸውን የትምህርትና የስልጠና መርሀ-ግብሮች ተከታትለው ላጠናቀቁ እጩ ምሩቃን የምስክር ወረቀትና እንደ ተገቢነቱ በሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 ሌሎች ተዛማጅ ህጐች መሠረት ዲፐሎማ ወይም ዲግሪ ይሰጣል፤
የራሱን የትምህርትና ስልጠና አሰጣጥ በየጊዜው ለማሻሻልም ሆነ የክልሉን መንግስታዊ ተቋማት የማስፈፀም አቅም ለመገንባት የሚረዱ የጥናትና የምርምር ስራዎችን ያካሂዳል፤
ከመንግስታዊ መ/ቤቶች ወይም ተቋማት፣ ከመንግስት የልማት ድርጅቶችና ከግሉ ዘርፍ በሚቀርብለት ጥያቄ መሰረት በአመራር ፍልስፍናና በሥነ-ምግባር ግንባታ ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችንና የምክር አገልግሎቶችን ይሰጣል፤
በየጊዜው የሚሰጣቸውን ትምህርትና ስልጠናዎች በተመለከተ የግምገማና የምዘና ሥርዓት ቀርጾ በተግባር ላይ እንዲውል ያደርጋል፤
በክልሉ መንግስት መስሪያ ቤቶች የሚያገለግሉ ባለሙያዎችን የሥራ አመራር ብቃት ለማጎልበትና ለማሳደግ የሚረዱ የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ ስልጠናዎችን ይነድፋል፣ ያሰለጥናል፣
በጥናትና ምርምር ስራዎች የተገኙ ውጤቶችን ያሳትማል፣ ለተጠቃሚዎች ያሰራጫል፤
ቦርዱ በሚያወጣቸው የምልመላ መስፈርቶች መሰረት ሰልጣኞችን ይቀበላል፣ የዕለት ተዕለት ግንባታቸውን በቅርብ ይከታተላል፤
በስሩ የተለያዩ የትምህርት፣ የስልጠና፣ የጥናትና የምርምር ክፍሎችን ያቋቁማል፣ የቤተ-መፃሀፍትና የቤተ-ሙከራ አገልግሎቶችን ያደራጃል፣ ተፈላጊ ግብዓቶች እንዲሟሉላቸው ያደርጋል፤
ሰልጣኞች የተሰጣቸውን ስልጠና አጠናቀው ወደየስራቦታቸው ሲመለሱ የሚኖራቸውን አፈፃፀም በቅርብ ይከታተላል፣ የስልጠና ዉጤታማነት ጥናት ያካሂዳል፣ ግኝቱን በተመለከተ ለሚመለከተዉ አካል ሪፖርት ያደርጋል፣ ከዚሁ በመነሳት የተሻሉ የአሰራር ስልቶችን ይቀይሳል፤
የተለያዩ ትምህርታዊ ሴሚናሮችን፣ ወርክ ሾፖችን፣ ኮንፈረንሶችንና አውደ- ጥናቶችን ያዘጋጃል፣ ያካሂዳል፣ ጥሪ ሲደረግለትም በንደነዚህ ዓይነት መድረኮች ይሳተፋል፤
አቻዎቹ ከሆኑና ተቀራራቢ ዓላማ ካላቸው የክልልና የፌደራል መንግስት ተቋማት ጋር የስራ ግንኙነቶችን ይመሰርታል፣ በትብብር ስልጠና ይሰጣል፣ ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መርሆዎችና ዓላማዎች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ በዉጭ ሀገር ከሚገኙ መሰል የስልጠናና የምርምር ተቋማት ጋር ሊገናኝና ተሞክሮዎችን ሊለዋወጥ ይችላል፤
የሥራ አመራር ሥልጠና፣ የምክር አገልግሎትና የጥናት ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት ገቢ የሚያገኝባቸዉን ሁኔታዎች ያመቻቻል፣ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች እንደአስፈላጊነቱ ተመጣጣኝ ዋጋ ያስከፍላል፤
የንብረት ባለቤት ይሆናል፣ ዉሎችን ይዋዋላል፣ በስሙ ይከሳል፣ ይከሰሳል፤
ዓላማዎቹን ከግብ ለማድረስ የሚረዱ ሌሎች ተዛማጅ ተግባራትን ያከናውናል፡፡